በሃዋሳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ውስጥ የተከሰተ ግጭት በተመለከተ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ!
(አዲስ አበባ፣ ኅዳር 04፣ 2018 ዓ.ም.)
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በሃዋሳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በሚገኘው ቶዮ ሶላር ኩባንያ ውስጥ የተፈጠረው ግጭት የማጣራት ስራውን አጠናቋል።
የግጭቱ መንስኤ “በስራ ገበታ ላይ በተደጋጋሚ በሰአቱ አልተገኘህም” በሚል በአንድ የውጭ ዜግነት ያለው ሱፐርቫይዘርና ኢትዮዽያዊ ሰራተኛ መካከል የተፈጠረ አምቧጓሮ መሆኑን ለመረዳት ችለናል።
አለመግባባቱ መፈታት የነበረበት የሰራተኞችን ሰብአዊ መብት በጠበቀ መልኩ በህግና በድርጅቱ ፓሊሲ እንጂ በፀብ መሆን እንዳልነበረበት መግባባት ላይ ተደርሷል። በመሆኑም በዚህ ክስተት ውስጥ ችግሩ እዚህ ደረጃ ላይ ሳይደርስ እንዲፈታ በወቅቱ ሀላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ 5 ሀላፊዎች ላይ ኩባንያው እርምጃ ወስዷል።
1) በግጭቱ ቀጥተኛ ተሳትፎ የነበረውን የውጭ አገር ሰራተኛ የድርጅቱ የስነምግባር መመሪያ ባለማክበር እንዲሁም
2) ጉዳዪ የሚመለከተው የኩባንያው የስራ ሀላፊ ድርጊቱ በተፈፀመበት ወቅት ተገቢውን አስተዳደራዊ ክትትልና እርምጃ ባለመውሰዱ ምክንያት ከሥራ አሰናብቷቸዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ተጨማሪ ሶስት መካከለኛ ደረጃ ሥራ አስኪያጆችም ሀላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው ምክንያት ከባድ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል። በዘላቂነትም እንደዚህ አይነት ችግሮች እንዳይደገሙ ስልጠናዎች ለኩባንያው ሰራተኞችና አመራሮች በቀጣይ የሚሰጥ ይሆናል።
ይህ ውሳኔ ቶዮ ሶላር ካምፓኒ ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ለማንኛውም ዓይነት የስነምግባር ጉድለት፣ አካላዊና ስነልቦናዊ ጥቃት እንደማይታገሱ አመላካች ነው።
በዚህ አጋጣሚ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በሚያስተዳድራቸው አስር ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች፣ አንድ ነፃ የንግድ ቀጠና እና ሶስት ፓርኮች የተቀናጀ መሰረተ ልማት ለባለሀብቶች እያቀረበ የሚገኝ ሀገራዊ ተቋም ነዉ። ተቋሙ በሚያስተዳድራቸው ሁሉም ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች እና ፓርኮች ውስጥ ለወጣቶች ሰፊ የስራ እድል እንዲፈጠር ከሚሰራው ስራ ጎን ለጎን የሠራተኞች ደህንነት፣ ክብር እና እኩልነት በማንኛውም አይነት ሁኔታ እንዳይጓደል ጥረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል በዚሁ አጋጣሚ ለማረጋገጥ ይወዳል።
ቶዮ ሶላር ለ2 ሺ ሰራተኞች የስራ እድል የፈጠረ በየወሩ ከ15 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኤክስፖርት እያደረገ ያለ ድርጅት ነው።