በኢትዮጵያ ዉስጥ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ተብለዉ የሚታወቁ ወደ አርባ (40) ድርጅቶች ሲኖሩ ከለዉጡ መንግስት የፖለቲካና ኢኮኖሚ ሪፎርም በፊት በመንግስት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር(Public Enterprises Holding Agency/PEHA) ክትትልና ቁጥጥር ስር ሆነዉ አስተዳዳሪ ቦርድ እየተሾመላቸዉ ባለቤትነታቸዉም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግስት( የገንዘብ ሚኒስቴር) ሆኖ በኢኮኖሚዉ ዉስጥ ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል፡፡ የሪፎርም መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣ በኃላ እነዚሁ የልማት ድርጅቶች፡ በአንድ ሆልዲንግ ኩባንያ (በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ኩባንያ) ስር እንዲተዳደሩ በማድረግ የአንድ ሉዓላዊ ሃብት/Soveriegn wealth fund) ተቀጥላ ድርጅቶች ሆነዉ እንዲሰሩ በአዲስ መልክ ተዋቅረዋል፡፡
በዚህ ፅሁፍ ዉስጥ፡ የልማት ድርጅቶቹ ከመንግስት ልማት ድርጅቶች ይዞታ ኤጀንሲ አስተዳደር ወደ ሆልዲንግ ኩባንያዉ የተዘዋወሩበትን የህግ ሂደት የለዉጡ መሰረታዊ አንድምታዎች፡እና በአንድ ሉዓላዊ ሃብት/ Soveriegn wealth fund) ስር መተዳደር የሚያስገኛቸዉ ጠቀሜታዎች እና በአጠቃላይ እነዚህ ተቋማት በሀገረ-መንግስት ግንባታ ላይ ያላቸዉን ሚና በንፅፅራዊ ዕይታ ይዳሰሳል፡፡
በብዙ የዓለም ሀገራት እንደሚታወቀዉ የሉዓላዊ ሀብት ፈንዶች የፋይናንስ እና ኢንቨስትመንት ወይም፡ የማህበራዊና ፖለቲካዊ ፖሊሲ ግቦች ማሳኪያ ተደርገዉ ወይም ሁለቱንም ግቦች ለማሳካት ታልሞ ሊመሰረቱ ይችላሉ፡፡ የሉዓላዊ ሃብት ፈንዶች የሚቋቋሙባቸዉ ጥቅል ዓላማዎችን ስንመለከት ለመጪዉ ትዉልድ ሃብትና ጥሪት ለማቆየት፣ የሃገርን ኢኮኖሚ ለማረጋጋት እና የሃብት ስብጥርን ለማብዛት ናቸዉ፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ኩባንያን የሚያቋቁመዉ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 478/2014 በመግቢያዉ ላይ፡ የኢዮጵያን ኢኮኖሚ ስትራቴጂካዊ ፍላጎቶች ለማሟላት፡የግል ኢንቨስትመንት ከመንግስት ጋር ለመስራት የሚያስችል ተቋማዊ አደረጃጀት መፍጠር፡የመንግስት የልማት ድርጅቶች ላይ ተገቢዉን የቁጥጥር ስርዓት በመዘርጋት የተሟላና ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዲያስገኙ ስርዓት መዘርጋት፡ ተገቢዉን የገበያ ስርዓት የተከተለ፡ ጠንካራና መልካም የኩባንያ አስተዳደር መፍጠር እና ከፍ ያለ ኢንቨስትመንትና ቴክኖሎጂ መሳብ በማለት ሆልዲንግ ኩባንያዉን ማቋቋም ያስፈለገበትን አመክንዮ ያስቀምጣል፡፡
በደንቡ ዓላማ አንቀፅ 5 ስር፡ የሚያስቀምጠዉም፡ ሆልዲንግ ኩባንያዉ፡ የመንግስት ስትራቴጂካዊ የኢንቨስትመንት ተቋም ሆኖ፡ የኩባንያዎች መልካም አስተዳደር፡መርሆዎችን መከተልና፡ ጥምር ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት፡ መደላድል መፍጠር እንደሆነ ይደነግጋል፡፡
ከደንቡ መግቢያና ዓላማዉን ከሚደነግገዉ አንቀፅ 5 መረዳት እንደሚቻለዉ የኩባንያዎች መልካም አስተዳደር ስርዓት መዘርጋት እና የመንግስት ስትራቴጂካዊ የኢንቨስትመንት ተቋም የሚሉ ፍሬ ነገሮችን እንገነዘባለን፡፡ የኩባንያዎች መልካም አስተዳደር ሲባል የራሱን የሆልዲንግ ኩባንያዉንና፡በስሩ ያሉ ተቀጥላ ኩባንያዎችን የሚመለለከት መሆኑ እሙን ነዉ፡፡ ይህ የደንቡ ዓላማ ድንጋጌ ከሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም አጀንዳ ጋር የሚስማማ ሲሆን ይኸዉም በሪፎርም አጀንዳዉ የፐብሊክ ሴክተር ፋይናንስና የመንግስት ልማት ድርጅቶች ሪፎርም ስር የመንግስት የልማት ድርጅቶችን መዋቅራዊ ለዉጥ ማድረግ አስፈላጊነት እንዲሁም የህግ፡ የመዋቅራዊ እና አስተዳደራዊ ስርዓቶቻቸዉን ማዘመን አስፈላጊነት ያስቀምጣል፡፡
ሉዓላዊ ብሄራዊ ሃብት ፈንድ እያደገ እየመጣ ያለ በኢኮኖሚ ዉስጥ ክፍተቶችን እየለየ የሚሞላ እንዲሁም የረጂም ጊዜ የፋይናንስ ግቦችን የሚያሳኩ እና ዘላቂ እና አካታች ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚያስችሉ የተቋማት ስብስቦች ናቸዉ፡፡ በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ስርዓት ዉስጥ እንደ ክፍተት ይታይ የነበረዉን የካፒታል ገበያ፡ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ አማካይነት የካፒታል ገበያ ባለስልጣንን በማቋቋም የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያን እዉን ማድረግ መቻሉ አንዱ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነዉ፡፡ በዚህም በኢትዮጵያ የተለያዩ ኩባንያዎች ምስረታ ሂደት፡ በዘፈቀደ በግለሰቦችና ቡድኖች የሚዘወር ከነበረበት፡ ስርዓታዊ እና ተቋማዊ በማድረግ የኩባንያዎች አደራጆች ከህዝቡ ገንዘብ ከመሰብሰባቸዉ በፊት ሊያሟሉአቸዉ የሚገቡ ህጋዊ ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ የካፒታል ስብሰባዉ ለህዝቡ ወይም ኢንቨስተሩ ገንዘብ ጥበቃና ዋስትና መስጠት የሚያስችለዉ ልምምድ በሀገራችን ተጀምሯል፡፡ ይህም ሆልዲንግ ኩባንያዉ በሀገራችን ከፍተትን ለይቶ በመሙላት ረገድ ካሳካቸዉ ግቦች መካከል አንዱ ነዉ ማለት ይቻላል፡፡
የመንግስት ልማት ድርጅቶች በሆልዲንግ ኩባንያ ስር ከመዋቀራቸዉ በፊት ድጋፍ፡ቁጥጥርና ክትትል ሲደረግላቸዉ የነበረዉ፡ በመንግስት ልማት ድርጅቶች አስተዳደር ኤጀንሲ የነበረ ሲሆን፡ ኤጀንሲዉ በዋናነት፡ የቦርድ አመራር፡መመደብ፡እቅድና አፈፃፀም ላይ ድጋፍና ክትትል ማድረግ፡ አለፍ ሲልም ምክረ ሃሳብ መስጠት ላይ የተወሰነ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በአዲሱ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ኩባንያ ስር ሲተዳደሩ፡ ግን፡ የሆልዲንግ ኩባንያዉን ስትራቴጂክ ግብ ሊያሟላ በሚችል መልኩ፡እና እንደ ተቀጥላ ድርጅቶቹ ባለቤት፡ ጥብቅ፡ ቁጥጥር፡ እና ክትትል ከማድረጉም በላይ፡ በሚፈለገዉ መልኩ አስተዳደራዊ ስርዓቶቻቸዉን በዘመናዊ የኩባንያ መልካም አስተዳደር፡እንዲመሩ ያስገድዳል፡፡ በቀድሞዉ ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ስር፡አብዛኞቹ ተቋማት በዋናነት እንደ መንግስት ፖሊሲ ማስፈፀሚያ የሚታዩ ሲሆን፡ በሆልዲንግ ኩባንያዉ አስተዳደር ስር ከገቡ በኃላ፡ ግን ተቋማቱ፡ እንደ ስትራቴጂክ የንግድና ኢንቨስትመንት ተቋም፡የሚታዩ ናቸዉ፡፡ምንም እንኳን ይሄም ቢሆን ከመንግስት ጥቅል ፖሊሲ ማዕቀፍ የሚወጣ ባይሆንም፡ መሰረታዊ ዕይታዉ ግን ዘመናዊ ንድና ኢንቨስትመንት ነዉ፡፡ በዚህ የተነሳም፡ የድርጅቶቹ/የተቀጥላ ኩባንያዎች/ የፋይናንስ ስርዓት ጤናማነት፡ ትርፋማነት፡ የኦዲት ወቅታዊነት፡ ዘመናዊ የሰዉ ሃብት አስተዳደር፡ በቴክኖሎጂ የታገዘ፡የተቋማት ሃብት አመራር፡ እንዲሁም፡ ኢንቨስት የሚያደርጉባቸዉ አዳዲስ ፕሮጀክቶች፡ አዋጭነት፡በጥብቅ የሚታዩ መለኪያዎች ናቸዉ፡፡በኩባንያ መልካ አስተዳደር እይታ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ስኬቶች መካከል የተቀጥላ ኩባንያዎቹ የኦዲት ተጎታችነት(ወቅታዊ አለመሆን) አንዱ ችግርና ተቀጥላ ኩባንያዎቹ፡ ሶስትና ከዚያ በላይ በጀት ዓመታት ወደ ኃላ የተጎተተ( የዘገየ) ኦዲት የነበራቸዉ ሲሆን፡ ይህም በሆልዲንጉ ስር መተዳደር ከጀመሩ በኃላ፡ ከፍተኛ ለዉጥ አምጥቶ አብዛኞቹ ተቀጥላ ድርጅቶች፡ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ኦዲትን ወቅታዊ ለማድረግ እንዲችሉ ማድረጉ ነዉ፡፡ ወቅታዊ ከማድረግ በተጨማሪ፡ የኩባንያ መልካም አስተዳደር አንዱ መለኪያ የሆነዉ፡የኦዲት መግለጫ፡ማዉጣት/Disclosure) ዉጤታማ እየሆነ እንዲመጣ አስችሏል፡፡
ሆልዲንግ ኩባንያዉ በስሩ የያዛቸዉ ተቀጥላዎች፡ ከሲቪል ሰርቪስ እሳቤ በመዉጣት፡ የሚለኩት፡ዕድገት አምጪ በሆኑ የፋይናንስ፡ የኦፕሬሽናል ልህቀት፡ የኩባንያ መልካም አስተዳደር፡ ብዙ የኮርፖሬት አስተዳደር እና ሌሎች ስትራቴጂካዊ መለኪያዎች መሆኑ፡ ተቀጥላዎቹ ሳይወዱ በግድ ወደ ዘመናዊ የኩባንያ መልካም አስተዳደር ስታንዳርድ እንዲገቡ እያደረጋቸዉ ይገኛል፡፡
የኩባንያ መልካም አስተዳደር መርህን መጎናፀፍ የንግድ ህጋችንም ሆነ በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ደንቦች በዝርዝር እንደተመለከተዉ የገንዘብ ገበያ ላይ ለመሳተፍ፡የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልተዉ ስለሚገኙ እና ለባለገንዘቦች በቂ የህግ ጥበቃና ዋስትና ስለሚያረጋግጥ፡በካፒታል ገበያ ላይ ለመሳተፍ እና የሚፈለገዉን ካፒታል ለማሰባሰብ ቀላል እና ተመራጭ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህንኑ በሚያረጋግጥ መልኩ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባወጣዉ የቻይና የመንግስት ልማት ድርጅቶች ሪፎርም ሀተታዉ፡በቻይና ሻንጋይ የገንዘብ ገበያ(ስቶክ ኤክቼንጅ) ላይ ሊስት ከተደረጉ ግዙፍ አስር/10 ኩባንያዎች መካከል ስምንቱ (8)፡ የቻይና መንግስት ልማት ድርጅቶች እንደነበሩ ይገልፃል፡፡ በኢትዮጵያም ሁኔታ ስንመለከተዉ ገና በታዳጊ ገበያ የሚታይ ቢሆንም በኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ገበያ/ Ethiopian Securities Exchange/ESX/ ላይ ሊስት ከተደረጉት ኩባንያዎች መካከል የኢንቨስትመንት ሆልደዲንግ ተቀጥላ የሆነዉ ኢትዮ ቴሌኮም ከቀዳሚዎቹ አንዱ መሆኑ ማሳያ ነዉ፡፡
የዘመናዊ የኩባንያ መልካም አስተዳደር ትሩፋቶች መካከል፡ የኢንቨስትመንት ስበት አቅም፡ማደግ፡ በትላልቅ ግዙፍ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች እምነት፡ማግኘት፡ ሀገራዊ የኢንቨስትመንት አቅም ማጎልበት፡የዉጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ማደግ ተጠቃሽ ናቸዉ፡፡ በዚህ ትግበራ የተነሳ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ኩባንያ እመርታዊ ዉጤቶች እየታዩ ሲሆን በአጭር ጊዜ ዉስጥ ከጃፓኑ ቶፓን ኩባንያ ጋር በሽርክና ወደ ስራ የገባዉ የሚስጢራዊ ህትመቶች ድርጅት፡ በቅርብ ጊዜ፡ የመሰረት ድንጋይ የተጣለለት ከዳንጎቴ ግሩብ ጋር የሚገነባዉ ማዳበሪያ ፋብሪካ እና ሌሎችም፡ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት፡ ዓለም አቀፍ የቢዝነስ አሰራርን፡ የግድ መዳበር፡ በንግድ ህግ፡መመራትን፡ ትርፋማነትን፡ዘመናዊ የኩባንያ አስተዳደርን እያሰረፁ የሚገኙና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ መመስረት እና በስር ያሉ ኩባንያዎች፡እመርታ ማሳያዎች ናቸዉ፡፡
የቻይና መንግስት ሉዓላዊ ሃብት ፈንድ የሆነዉ ቻይና ኢንቨስትመንት ኮርፖሬሽን በቻይና እና በሌሎች አገሮች ለሚደረጉ የቻይና መንግስት ስትራቴጂክ ኢንቨስትመንቶች ዋናዉ ተቋም ሲሆን በተለይም ተቀጥላዉ በሆነዉ ሴንትራል ሁዊጂን አማካኝነት፡በባንክ ኦፍ ቻይና፡ ቻይና ኮንስትራክሽን ባንክ በመሳሰሉት የፋይናንስ ተቋማት ቀጥተኛ እና ኢ-ቀጥተኛ የሆነ ቁጥጥር በማድረግ፡የመንግስት ስትራቴጂክ ኢንቨስትመንት ተቋም ሆኖ ያገለግላል፡፡ በተመሳሳይ የህንዱ ብሄራዊ ኢንቨስትመንት እና መሰረተ ልማት ፈንድ የተቋቋመዉ፡በህንድ መንግስት ስትራቴጂክ ኢንቨስትመንቶች ላይ ለመሳተፍ፡ ነዉ፡፡ የኳታር ኢንቨስትመንት ፈንድ/ኳታር ኢንቨስትመንት ባለስልጣን/;አንዱና የዓለማችን ግዙፍ ከሚባሉት ዉስጥ ተጠቃሽ ሲሆን፡ ዋና ዓላማዉም፡ በተለያዩ ዓለም ባሉ የተለያዩ ሴክተሮችና ገበያዎች ላይ በመሳተፍ/ኢንቨስት በማድረግ) ለሀገሪቱና ቀጣይ ትዉልዳቸዉ፡ሃብትና እሴት መፍጠር ነዉ፡፡በተመሳሳይ የራሽያን የኢኮኖሚ ሪፎርም እዉን በማድረግ ሂደት ዉስጥ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱት ግዙፎቹ የኤሮስፔስ አምራች፡ በግብርና የተሰማራዉ፡ ፎስ አግሮ፡ በሃይል እና ኬሚካል ላይ የተሰማራዉ ዛፕስ እና ሌሎችም በተመሳሳይ የሉዓላዊ ሃብት ፈንድ መዋቅር ስር ሚገኙ ናቸዉ፡፡
ብሄራዊ ሉዓላዊ ሃብት ፈንድ በአንድ ሀገር ዉስጥ የመንግስት ስትራቴጂክ ኢንቨስትመንት፡ተቋም ሆኖ ከማገልገል ባለፈ፡ ማህበራዊ ፖሊሲና ርትዕ ማሳኪያ መሳሪያዎችም ናቸዉ፡፡ የኢትዮጵያ ተነጻጻሪ አቅሞች፡ በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም ተለይተዋል፡፡ የተለዩት እምቅ ብሄራዊ አቅሞችም፡ ማዕድን፡ ግብርና፡ ቱሪዝም፡ ኢንዱስትሪ እና አይሲቲ ዘርፎች እንደሆኑ፡ተመላክቷል፡፡በነዚህ የተለዩ እምቅ አቅሞች ላይ ያለንን የህዝብ ብዛት(የሰዉ ሃብተ)፡ መልክዐምድራዊ ተመራጭነት፡ ተጨምሮበት፡ አምቅ አቅምን ወደ ተጨባጭ እቅም በመለወጥ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ በኩል እየተጠናከረ የመጣዉ የኩባንያዎች መልካም አስተዳደር፡ ተጨምሮበት፡ በሀገር ዉስጥ ያለንን ሃብትና ኢንቨስትመንት ከማሰባጠር ባለፈ በቀጠናችን ባሉ አገሮች ጭምር፡ በፋይናንስ፡ በመሰረተ ልማት ግንባታ እና ሌሎች ዘርፎች ለመሳተፍ፡ ሆልዲንግ ኩባንያዉ ምቹ መደላድል እየፈጠረ ያለ ለመጪዉ ትዉልድ ጥሪት እና ተስፋ የሚሰጥ እና በሌሎች ሀገራት እንዳየነዉ፡የመንግስት ልማት ድርጅቶች ለሀገረ መንግስት ግንባታዉ የማይተካ ሚና የሚጫወቱ መሆናቸዉን የሚያረጋግጥ እዉነታ ነዉ፡፡ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዉጤታማ አመራር የተጀመረዉ የልማት ድርጅቶች ጎልብተዉ፡ከሀገር ዉስጥ ኢንቨስትመንት አልፎ፡ በቀጣናችን ባሉ ሀገሮች፡ተወዳዳሪ እና ዓለም አቀፍ ፕሮጀክቶች ላይ የሚሳተፉ ኩባንያዎችን የምናይበት ጊዜ ቅርብ መሆኑን የሚያሳይ ጎዳና ላይ እንገኛለን፡፡
ዓለማየሁ ሰይፉ
ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን