በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችና ኢንዱስትሪ ፓርኮች አስተዋጽኦ እና ተግዳሮቶች ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ተካሄደ
በኢትዮጵያ የሚገኙ ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለሀገር ልማት ያበረከቱትን አስተዋጽኦ እና ሊያጋጠሙ በሚችሉ ተግዳሮቶች ዙሪያ ትኩረቱን ያደረገ የምርምር ወርክሾፕ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ(ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች እና ኢንዱስትሪ ፓርኮች የሃገርን እድገት በማፋጠን በሥራ ዕድል ፈጠራ ፣በውጪ ምንዛሬ ግኝት፣ በተኪ- ምርት እና ክህሎት በመፍጠር ረገድ የራሳቸውን አሻራ ማኖራቸውን ገልጸው ለሠራተኞች ምቹ የስራ ከባቢ ለመፍጠር እና ገቢያቸውን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል ብለዋል።
ዶ/ር ፍሰሃ በተጨማሪም አሁን ላይ በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች እና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ያለውን የክህሎት እድገት እና ቴክኖሎጅ ሽግግር በሚፈለገው ደረጃ ለማሳደግ በዘርፉ የተሰማሩ ፖሊሲ አውጪዎች እና ባለድርሻ አካላት የምርምር ውጤቶቹን መነሻ በማድረግ የሠራተኛውን ክህሎት ለማሳደግ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በምክክር መድረኩ በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚሰሩ ሠራተኞችን ምርታማነት ለመጨመር እና የሥራ እርካታ ለማሳደግ ከደመወዝ ባሻገር ለሠራተኞች የሥራ ዕውቅና መስጠት፤የሙያ ዕድገት የሚያገኙበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር፤የሰራተኞች የስራ አካባቢ ምቹ ማድረግ፣ ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር እና የኢኮኖሚ ትስስር ማስፋት እንደሚገባ በቀረበው ጥናታዊ ጽሁፎች ተመላክቷል።
በምክክር መድረኩ ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ኮንፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ አሰሪዎች ማህበር፣ የዓለም ሠራተኞች ማህበር (ILO) እና የጀርመን ተራድኦ ድርጅት (GIZ) ተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን በመድረኩ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚታዩ ስኬቶችን ለማስቀጠል እና ተግዳሮቶችን ሳይንሳዊ ምርምሮችን መሰረት በማድረግ ለመፍታት የሚያስችል ጠንካራ መነሻ ሃሳቦች ሀገር ውስጥ እና ውጪ ሀገር ባሉ ምሁራን የምርምር ውጨቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በአሁኑ ወቅት በመላ ሀገሪቱ የሚያስተዳድራቸውን 14 የኢንቨስትመንት ማዕከላት ከ85 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል፤ከ290 በላይ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶችን በማሳተፍ የሃገር እድገት ላይ የራሱን ኣሻራ በማሳረፍ ላይ ይገኛል።
ኮርፖሬሽኑ ከሚያስተዳድራቸው ልዩ ኢከኖሚ እና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ጨምሮ 24 በመንግስት እና በግል ዘርፍ የለሙ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በስራ ላይ ሲሆኑ ከአንድ ደርዘን በላይ ተጨማሪ ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ከኢትዮጵያ ኢንቨትመንት ኮሚሽን ፍቃድ ወስደው ወደ ስራ ለመግባት ጥረት እያደረጉ መሆኑ ተገልጿል፡፡
HKJP21D0s3OEB30