ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪና የሁሉንም የኢንቨስተሮችን ፍላጎት ማሟላት የሚችሉ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችን መገንባት መቻሏ ተገለጸ
ኢትዮጵያ ባለፉት 11 አመታት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ሁሉንም አይነት ኢንቨስትመንት ተቀብለው ማስተናገድ የሚችሉ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ገንብታ ባለሃብቶችን በማስተናገድ ላይ መሆኗን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኦፐሬሽንና ፓርክ አስተዳደር ዘርፍ ስራ አስፈፃሚ አቶ ፍፁም ከተማ ገለፁ፡፡
ስራ አስፈፃሚው ይህን የገለፁት “ኢንቨስት ኢን ኢትዮጵያ 2026” በተሰኘው ፎረም ላይ ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች እና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለውጭ ንግድ ዘርፍ እድገት ያላቸው ሚና ላይ በተዘጋጀ የፓናል ውይይት ላይ ነው፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በዘርፉ ውስጥ የቆየው ለ11 ዓመታት ያህል ቢሆንም፣ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ እንደ ቻይና ያሉ ሀገራትን ስኬታማ ተሞክሮ በመውሰድ፣ በመላ ሀገሪቱ 14 ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችና የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ገንብቶ በማስተዳደር ላይ መሆኑን አቶ ፍፁም ከተማ ጠቁመው በውጭ ምንዛሬ ግኝት፣ በስራ እድል ፈጠራ፣ በተኪ ምርት፣ በገበያ ትሥስር፣ እንዲሁም በእውቀትና ቴክኖሎጅ ሽግግር ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ጠቅሰዋል።
ኮርፖሬሽኑ አሁን ላይ የሚያስተዳድራቸውን ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ሃገራዊ ተልእኳቸውን ለማጠናከር ኮርፖሬሽኑ አሰራሩን ቀልጣፋ እና ምቹ የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዝናቡ ይርጋ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ጠንካራ፣ ሳቢ፣ የተረጋጋና ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ ለመፍጠር በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰው ማነቆ የነበሩ የኢንቨስትመንት ፖሊሲዎችን የማሻሻል፣ በልዩ ዞኖቹ ውስጥ ለሚሰሩ ባለሀብቶች ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮችና ዕድሎች የማመቻቸት ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ የተሰሩ ስራዎችንና በሃገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ያላቸውን አበርክቶ በተመለከተ ለፎረሙ ተሳታፊዎች በኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አማካሪ አቶ አለማየሁ ሰይፉ ገለፃ ተደርጓል።
በመድረክ ላይ በቂሊንጦ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን እና በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ውስጥ ስራ የጀመሩት አፍሪ ኪዩር ማኑፋክቸሪንግ እና ሞሃን ፒኤልሲ የተሰኙ ሁለት ኩባንያ ስራ አስኪያጆች ያላቸውን ተሞክሮ ለፎረሙ ተሳታፊዎች አካፍለዋል።
በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ከፍተኛ ልምድ እና ተሞክሮ ያላቸው የተለያዩ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች፣ የኩባንያ ባለቤቶች፣ የኢንቨስትመንት አማካሪዎች እና የንግድ ተወካዮች የተሳተፉበት መድረክ ዛሬ ተጠናቋል፡፡
መድረኩ በኢትዮጵያ ኢንቨትመንት ኮምሽን በየአመቱ የሚዘጋጅ ሲሆን ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ መካሄዱ ይታወቃል፡፡