በቦሌ ለሚ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የመሶብ አገልግሎት ሞዴል ግንባታ ሥራ ተጀመረ
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ሥር በሚተዳደረው በቦሌ ለሚ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የኢንዱስትሪ መሶብ አገልግሎትን ለማስጀመር የቢሮ ማደራጀትና ማስተካከል ሥራ ተጀመረ።
ሥራው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መሶብ አገልግሎት ሞዴልን መሠረት በማድረግ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለመስጠት ያለመ ነው።
የኢንዱስትሪ መሶብ አገልግሎትን በኮርፖሬሽኑ ሥር በሚተዳደሩ ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖችና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለማስጀመር ቦሌ ለሚ ልዩ ኢኮኖሚ ዞንን እንደ ማሳያ ለመጠቀም ታቅዷል።
ለዚህም የሚያስፈልጉ የሕንፃ አደረጃጀት፣ የቴክኖሎጂ፣ የአገልግሎት እና የሰው ኃይል ዝግጅቶች ያሉበት ደረጃ በኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍፁም ከተማ እና በፌዴራል መሶብ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዮናስ ዓለማየሁ በተገኙበት ተገምግሟል።
በቦሌ ለሚ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የተጀመረው የማዕከሉ ዝግጅት ሥራ በአጭር ጊዜ ተጠናቆ አገልግሎት እንደሚጀምር ይጠበቃል።
ከዚህ ማዕከል አፈጻጸም የሚገኘው ልምድና ተሞክሮ በመገምገም የኢንዱስትሪ መሶብ አገልግሎቱን ወደ ሌሎች በኮርፖሬሽኑ ሥር ወደሚገኙ ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖችና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለማስፋፋት ታቅዷል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን 14 ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖችንና ኢንዱስትሪ ፓርኮችን በሥሩ የሚያስተዳድር ሀገራዊ የልማት ተቋም ነው።
የፌዴራል መሶብ አገልግሎት በበኩሉ የመንግሥት አገልግሎቶችን በዲጂታል ሥርዓት በማቅረብ፣ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን፣ የዜጎችን እንግልትና የጊዜ ብክነት ለመቀነስ የሚሠራ መንግሥታዊ ተቋም ነው።
የኢንዱስትሪ መሶብ አገልግሎት መጀመር በኢንዱስትሪ ፓርኮችና ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ ለሚንቀሳቀሱ ባለሀብቶችና ኢንተርፕራይዞች የመንግሥት አገልግሎቶችን በተቀናጀና በቀላል መንገድ ለማድረስ አስተዋጽኦ ያበረክታል::