የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን በመደገፍ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ለሃገራዊ እድገት የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ስራዎች በመሰራት ላይ ናቸው:-ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር)
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በሚያስተዳድራቸው ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች እና ኢንዱስትሪ ፓርኮች የሃገር ውስጥ ባለሃብቶችን ተሳትፎ በማሳደግ የማኑፋክቸሪግ ዘርፉ ለሃገራዊ እድገት የበኩሉን ሚና እንዲያበረክት የሚያስችሉ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑን የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) ገለፁ።
ዋና ስራ አስፈፃሚው ይህን የገለፁት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ባዘጋጀው "ኢትዮጵያ ታምርት 2018 " ኤክስፖ ላይ የኢትዮጵያን የአምራች ዘርፍ የስራ ፈጠራ አቅም ለማሳደግ፡ የአመራር ሥርዓት፣ ዲጂታላይዜሽን እና የቤተሰብ ድርጅቶች ሚና" ላይ ትኩረቱን ያደረገ የፓናል ውይይት በተካሄደበት ወቅት ነው።
ዶ/ር ፍሰሃ በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት፤ ባለፉት አመታት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ለሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት ያለው ድርሻ ከ4 እስከ 6 በመቶ መሆኑን ጠቁመው የዘርፉ እድገት ከኢኮኖሚው እድገት ፍጥነት ጋር አለመጣጣሙን እና ይህንን ለማስተካከልም ኮርፖሬሽኑ በመላ ሀገሪቱ አልምቶ በሚያስተዳድራቸው 14 የኢንቨስትመንት ማእከላት የሃገር ውስጥ ባለሃብቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ በርካታ ስትራቴጂካዊ ለውጦችን እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ዶክተር ፍሰሃ በማብራሪያቸው፤ ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እድገት ዋነኛ ማነቆ የሆኑትን የመሬት፣ የመሰረተ ልማት እና የቢሮክራሲ ችግሮችን ለመቅረፍ ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች አስፈላጊ መሰረተ ልማቶችን ከማሟላት በተጨማሪ በአንድ ማዕከል አገልግሎት ደግሞ መሰረታዊ የመንግስት አገልግሎቶችን በማስገባት ለአምራች ኢንዱትሪው እድገት ትልቅ ድርሻ እየተወጣ መሆኑን አስረድተዋል።
ዋና ስራ አስፈፃሚው በመድረኩ የአንድ ሀገር የኢንዱስትሪ ሉዓላዊነትና ዘላቂነት የሚረጋገጠው የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ተሳትፎ ማሳደግ መሆኑን በመጥቀስ፤ ኮርፖሬሽኑ ለሀገር ውስጥ አምራቾች ቅድሚያ በመስጠት ወደ ኢንቨስትመንት ማእከላቱ እንዲገቡ እያበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።
ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው የኢንቨስትመንትም ማእከላትም ከዚህ በፊት በአልባሳትና ጨርቃ ጨርቅ ላይ ያተኮሩ ኢንዱስትሪዎች እንደነበሩ አብራረርተው ዛሬ ላይ ዘርፈ ብዙ ኢንዱስትሪዎችን መገንባት መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡ በአሁኑ ወቀት ወደ ኢንቨስትመንት ማዕከላቱ የሚገቡ ኢንቨስትመንቶች እንደ ሶላር ሃይል፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) እና ሮቦቲክስ ባሉ የላቁ ቴክኖሎጂዎች ላይ እንዲያተኩሩ በማድረግ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማፋጠን እየተሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮችንና ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችን ከብዛትና ከስርጭት ባለፈ በውጤታማነትና በጥራት ላይ በማተኮር፤ ከሎጅስቲክስ ኮሪደሮች ጋር በማስተሳሰር ምርታማነታቸውን ለማሳደግ የሪፎርም ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ዶ/ር ፍሰሃ በመድረኩ አብራርተዋል።
የቤተሰብ ድርጅቶችና ኢንተርፕራይዞች ወደ መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪነት እንዲሸጋገሩ ካፒታል፣ እውቀትና ዘመናዊ የአመራር ስርዓት እንደሚያስፈልጋቸው የጠቆሙት ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ ለዚህም ኮርፖሬሽኑ ምቹ ምህዳር መፈጠሩን ገልጸዋል።
በመጨረሻም "ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ የሀገር ውስጥ ምርትን በማሳደግና የውጭ ምንዛሬን በመተካት ረገድ ያለውን ሚና አድንቀው፤ ኮርፖሬሽኑ አምራች ዘርፉ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት እንዲሆን ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት 2018 በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አዘጋጅነት ከሚያዝያ 25 እስከ 30 በአዲስ ኮንቬንሽን ሴንተር እየተካሄደ ሲሆን ከ370 በላይ አምራቾች እየተሳተፉበት ይገኛል።