ኮርፖሬሽኑ በሀዋሳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የተለያዩ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶችን አስመረቀ
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ለሆቴልና አፓርትመንት አገልግሎት የሚውል አንድ ባለአምስት ወለል ሕንፃን ጨምሮ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በሀዋሳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን አስመረቀ።
በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኮርፖሬሽኑ የመሬትና መሠረተ ልማት ዘርፍ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጸጋዬ ዘካሪያስ እንደገለጹት፣ ለምርቃት የበቃው ሕንፃ 610 ካሬ ሜትር ስፋት ላይ ያረፈ ሲሆን 90 ስታንዳርድ ክፍሎችን ይዟል።
ምክትል ሥራ አስፈጻሚው እንዳሉት፣ ኮርፖሬሽኑ የገቢ ምንጩን ለማስፋት የጀመረውን የሆቴልና አፓርትመንት ሥራ የበለጠ እንደሚያጠናክረው ጠቁመዋል። ይህም ኮርፖሬሽኑ በአምስት ዓመት ስትራቴጂካዊ ዕቅዱ በግልጽ ያስቀመጠውን ዘርፈ ብዙ የገቢ ምንጭ የመገንባት ዕቅድ በተግባር እያሳካ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።
የሀዋሳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ሥራ አስኪያጅ አቶ ማቲዎስ አሸናፊ በበኩላቸው፣ ኮርፖሬሽኑ በልዩ ኢኮኖሚ ዞኑ 450 የሚጠጉ አፓርትመንት ቤቶችን አልምቶ ለባለሀብቶች እያከራየ እንደሚገኝ ገልጸዋል። አሁን የተገነባው ሕንፃም የኮርፖሬሽኑን የገቢ ምንጭ ከማስፋት ባሻገር ለሀዋሳ ከተማ ተጨማሪ የቱሪዝም አቅም እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።
ኮርፖሬሽኑ ካስገነባው አዲስ ሕንፃ በተጨማሪ አጠቃላይ ዕድሳት የተደረገላቸውን ሁለት ሕንፃዎች ለሥራ ዝግጁ አድርጓል። ለልዩ ኢኮኖሚ ዞኑ የሚያስፈልገውን የኃይል አቅርቦት የሚያጠናክር የማስፋፊያ ሥራም አከናውኗል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የገቢ ምንጩን ከማምረቻ ቦታ ኪራይና ከለማ መሬት ኪራይ በተጨማሪ ለማስፋት በማሰብ የተለያዩ ተግባራዊ እርምጃዎችን ወስዷል።
ከእነዚህ እርምጃዎች መካከል ኮርፖሬሽኑ አልምቶ የሚያስተዳድራቸውን ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖችና ኢንዱስትሪ ፓርኮች በራሱ አቅም ለማልማት የሚያስችለውን ራሱን የቻለ የኮንስትራክሽን ልማት ቢዝነስ በማቋቋም ወደ ሥራ አስገብቷል።
ዛሬ ለምርቃት የበቃውን ሕንፃም ይህ የኮርፖሬሽኑ የኮንስትራክሽን ልማት ቢዝነስ በአምስት ወራት ውስጥ ገንብቶ ለማጠናቀቅ ችሏል። የቦሌ ለሚ ልዩ ኢኮኖሚ ዞንን የሼድ ማስፉፊያ ስራን በመስራት ላይ ይገኛል።
በተጨማሪም ኮርፖሬሽኑ የገቢ ምንጩን ለማስፋት የጀመረው የሆቴልና አፓርትመንት ዘርፍ በሀዋሳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ውስጥ የነበሩ አፓርትመንት ሕንፃዎችን እያስተዳደረ ነው።
ኮርፖሬሽኑ በሎጂስቲክስና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለመሰማራትም የተለያዩ ዝግጅቶችን እያከናወነ ይገኛል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የሀዋሳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞንን ጨምሮ 14 ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖችና ኢንዱስትሪ ፓርኮችን በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች አልምቶ የሚያስተዳድር የመንግሥት የልማት ድርጅት መሆኑ ይታወቃል።
30