ኮርፖሬሽኑ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በታሪኩ ከፍተኛውን ገቢ ማስመዝገቡ ተገለጸ
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በተጠናቀቀው የ2018 በጀት ዓመት በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍተኛውን የገቢ መጠን ማስመዝገቡን የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) ገለጹ።
እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ፣ ኮርፖሬሽኑ በበጀት ዓመቱ ከ5.8 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ያስመዘገበ ሲሆን፣ ይህም ከተያዘው የገቢ ዕቅድ 90 በመቶ የተሳካ አፈጻጸም መሆኑን ገልጸዋል። በተጨማሪም የዘንድሮው የገቢ አፈጻጸም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 42 በመቶ እድገት እንዳሳየ ጠቁመዋል።
የገቢ መጠኑ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያድግ ከረዱት ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል በሁሉም ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ አሰራርን ቀልጣፋና ዘመናዊ ማድረግ፣ አዳዲስ የገቢ ማስገኛ አማራጮችን በትኩረት ማልማት እንዲሁም በየደረጃው ያለውን ቅንጅታዊ አሰራሮችን ማጠናከር በዋናነት ተጠቃሽ መሆናቸውን ዶ/ር ፍሰሃ አብራርተዋል።
በበጀት ዓመቱ ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከ70 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች አዲስ የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉንም ገልጸዋል።
በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ በኮርፖሬሽኑ በሚተዳደሩ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ባሉ ባለሀብቶች ተመርተው ወደ ውጭ ገበያ ከተላኩ ምርቶች 266.9 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ የውጭ ንግድ ገቢ መገኘቱ ተገልጿል።
በተጨማሪም ከ750 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የተመዘገበ የመነሻ ካፒታል ያላቸው 166 አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን መሳብ መቻሉም ከበጀት ዓመቱ ጉልህ ውጤቶች መካከል መሆኑ ተጠቅሷል።