ኮርፖሬሽኑ ከ750 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሉ ተገለጸ
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በ2018 በጀት ዓመት ከ750 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የሚገመት ኢንቨስትመንት ያላቸው 166 ባለሃብቶችን ወደሚያስተዳድራቸው ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችና ኢንዱስትሪ ፓርኮች መሳብ መቻሉን ገልጿል።
ይህ አፈጻጸም ከተያዘው ዕቅድ አንጻር 75 በመቶ መሆኑ የኮርፖሬሽኑ የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በሐዋሳ ከተማ እየተካሄደ ባለ የግምገማ መድረክ ላይ የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ፍሰሃ ይታገሱ ገልጸዋል።
በሪፖርቱ መሠረት፣ ወደ ኮርፖሬሽኑ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከተሳቡት ኢንቨስትመንቶች መካከል 84 በመቶው የሀገር ውስጥ፣ 10 በመቶው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት (FDI) ሲሆን፣ ቀሪው 6 በመቶ ደግሞ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች በጥምረት ያከናወኑት ኢንቨስትመንት መሆኑም ተብራርቷል።
ሪፖርቱ ባለሃብቶቹ የተሰማሩባቸው የሥራ ዘርፎች እንዲሁም የመጡባቸው ሀገራት የተለያዩ መሆናቸውን ያመለክታል። ከተሳተፉት አገራት መካከል ቻይና፣ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ህንድ እና ጅቡቲ ይገኙበታል።
በ2018 በጀት ዓመት የተሳቡት ኢንቨስትመንቶች በንግድና ሎጂስቲክስ፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በፋርማሲዩቲካልና በሕክምና መሣሪያ ማምረቻ፣ በአልባሳትና ጨርቃ ጨርቅ፣ በኬሚካልና ኮንስትራክሽን፣ እንዲሁም በኢንጂነሪንግና ብረታ ብረት ዘርፎች የተሰማሩ ባለሃብቶች መሆናቸውን ተመላክቷል።
ይህም ኮርፖሬሽኑ ባለ ብዘሃ ዘርፍ ኢንዱስትሪዎች በሚያስተዳራቸው ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች እና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ እንዲገቡ በአምስት አመት እስትራቴጂክ እቅዱ ያስቀመጠውን ግብ በእቅዱ የመጀመሪያ አመት ትግበራ እየተተገበረ መሆኑን እንደሚያመላክት ዋና ስራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ዘርፈ ብዙ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ለመሳብ ሲያቅድ ብዝሃነቱ በኢኮኖሚ ዘርፍ ብቻ ሳይሳሆን ባለሀብቶች በሚሳቡበት ሀገራት እና ባለቤትነት ጭምር እንደሚመዝን ያመላከቱት ዶ/ር ፍሰሃ ይህም በዓለም አቀፍ የንግድ ሰንሰለት ውስጥ ያልታሳበ ሁኔታ ሲያጋጥም ሊፈጠሩ የሚችሉ ሁኔታዎች መዛነፎችን ለመቋቋም እንደሚረዳ አብራርተዋል፡፡